የትግራይ ክልልን ጨምሮ የሰብአዊ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልልን ጨምሮ የሰብአዊ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጭ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተከታተለው የሚገኘውን ሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ስራን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበሩን ተከትሎ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የእለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቆ ድጋፉን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ድጋፍ በማድረጉ ሂደት እየተሳተፉ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ እስካሁን 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ለሚሆኑት ዜጎች ከ305 ሺህ በላይ ኩንታል የእህል ድጋፍ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም 22 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል በጥምረት እና 69 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ለሴፍቲኔት ተረጅዎች ለማድረስም በሂደት ላይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ እህል ነክ ያልሆኑ ድጋፎችም በስፋት እየደረሱ መሆሆኑን ገልፀዋል።
መንግስታዊ አገልግሎትን የማስጀመር ስራውም ተጠናክሮ እንደቀጠለ መሆኑን በመጥቀስም፥ 71 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎ የመድሃኒት አቅርቦት ለማድረስ ጥረት መደረጉንና የውሃ መስመሮች እስከሚጠገኑ በቦቴ ውሃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ትምህርት ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ የፀጥታ ሃይሉ እንዲጠናከርና ወደ ስራ እንዲመለስ መደረጉ ውጤት እየታየበት መሆኑንም አውስተዋል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ ለተፈናቀሉና ችግር ውስጥ ለሚገኙ ከ104 ሺህ በላይ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዞኑ ከሚገኙት 183 ቀበሌዎች ውስጥ ከሰላሳ ሁለቱ በስተቀር አብዛኛዎቹን ከታጣቂዎች የማጥራት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፤ በቀሪዎቹ ላይ የማጥራት ስራ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
በተጨማሪም ከማህበረሰቡ የተውጣጣ ሚሊሻ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ 9 ሺህ የሚሆኑት ወደ ስልጠና ይገባሉ ብለዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!