Fana: At a Speed of Life!

ከ19 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 47 የወደብ መሳሪያዎች ወደ ስራ ገቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞጆ ደረቅ ወደብ የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉ ከ19 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 49 የወደብ መሳሪያዎች በዛሬው እለት በይፋ ወደ ስራ ገብተዋል።

ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የተገዙት የመጀመሪያዎቹ የወደብ መሳሪያዎች ምረቃ ስነ-ስርዓትም በሞጆ ደረቅ ወደብ ተካሂዷል።

ምርቃት ስነ-ስርዓቱ  ላይ መልዕክት ያስተላለፉት  ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ÷ የወደብ መሳሪያዎቹ ወደ ስራ መግባት በወደቡ ቀልጣፋና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ  የዚህ ማዕከል አገልግሎት መጀመር ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለሎጀስቲክስ ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ደረቅ ወደቦችን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ያላቸውን ሚና ከወደብነት ባሻገር ለኢኮኖሚው እድገት ቁልፍ ድጋፍ ሊሆኑ የሚችሉ እሴት የሚጨምሩ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

አሁንም የሀገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ ለማጠናከር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረው÷የሎጅስቲክስ አገልግሎትን ለማሳደግም ትኩረት እንደተሰጠው  ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ዳግማዊት አያይዘውም ለዚህ ፕሮጀክት ስኬታማነት አሻራቸውን ላሳረፉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም  ቀሪ ስራዎች በተቀመጠለት ጊዜና የጥራት ደረጃ ቢቻል ደግሞ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ መጠናቀቅ እንዲችል  ባለድርሻ አካላት ከየትኛውም ጊዜ የላቀ ትብብራችሁን እና አጋርነታችሁን እንድታሳዩ ሲሉ  አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም  ማዕከሉ የተሟላ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

በአለም ባንክ የኢትዮጵያ  ዳይሬክተር አቶ ኦስማኔ ዲዮኔ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባቡር ትራንስፖርት ካላቸዉ ሀገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው የኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ ሎጀስትክስ ዉጤታማነት እንዲሻሻል እና እንዲቀላጠፍ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ አለም ባንክ  ዝግጁ መሆን አረጋግጠዋል።

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ  ሚንስትር ዴኤታዎችን ጨምሮ ከፌደራል እና ከአከባቢው መስተዳድር ከፍተኛ የመንግስት አካላት መገኘታቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.