ከ21 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በጮቢ ወረዳ የጮቢ ከተማ ጨምሮ በዙርያዋ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ21 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ተመረቀ፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ በፕሮጀክቱ ተቆፍረው አሁን ወደ ስራ ያልገቡ ጉድጓዶችን ወደ ስራ በማስገባት ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን በቀጣይ ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ተመርቆ ስራ የጀመረው ይህ ፕሮጀክት አሁን ላይ በአጠቃላይ 12 ቀበሌዎችን ተጠቃሚ አድርጓልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
ፕሮጀክቱ ከሃያ አንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ገንዘቡም ከልማት አጋሮች፣ ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሃ ልማት ኮሚሽን፣ ከክልሉ፣ ከዞኑና ከወረዳው አስተዳደር የተገኘ ነው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የአከባቢው ህብረተሰብም በፕሮጀክቱ ግንባታ ጉልበቱን ሳይሰስት በመስራቱ በገንዘብ ቢተመን እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጽዖ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ባለባቸው በሃገሪቱ ሁሉም አከባቢዎች የውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በበርካታ ቀበሌዎች ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የውሃውን መሠረት ልማት እንዲጠብቁት አሳስበዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!