የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሩሲያው አቻቸው ጋር በስልክ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በስልክ ተወያዩ፡፡
በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እና እየተደረገ ስላለው የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ ጥረት ለሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
አሁን ላይም በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ በኩል መሻሻል መታየቱን በመጥቀስም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የተሟላ ምላሽ ለመስጠትም ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ ደመቀ ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ ሂደት ለመፍታት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት በተመለከተም አብራርተዋል፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነዋል፡፡
አያይዘውም መንግስት በትግራይ ክልል የሚስተዋለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት ሩሲያ እንደምትረዳና እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡
ሩሲያም በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗንም አንስተዋል፡፡
ሰርጌ ላቭሮቭ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በንግድና ቢዝነስ ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ አውስተዋል፡፡
በንግግራቸውም የአፍሪካ እና ሩሲያን ግንኙነት ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል፡፡
አያይዘውም ሃገራቸው በፈረንጆቹ 2022 የሚካሄደውን የአፍሪካ ትሮይካ ሩሲያ ጉባኤ በአፍሪካ ምድር እንዲካሄድ ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ወቅት በተለያዩ ዘርፎች በሃገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!