የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል ያለውን ተጨባጭ ዕውነታ ያልተረዳ መረጃ ማውጣቱ አግባብነት የሌለው መሆኑንን መንግስት ገለጸ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል እየቀረበ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ከግንዛቤ ያላስገባ እና ተጨባጭ ዕውነታን ያልተረዳ መረጃ ማውጣቱ አግባብነት የሌለው መሆኑን መንግስት ገለጸ።
ህብረቱ ያወጣው መረጃ መንግስት በክልሉ እያቀረበ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ከግንዛቤ ያላስገባ እና በመረጃ ያልተደገፈ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምሽቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መንግስት በአካባቢው የህግ ማስከበር ስራን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህብረቱ የሚያወጣው መረጃ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ እና ተገቢነት የሌለው ነውም ብሏል።
በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከተፈጸመበት እለት አንስቶ በወንጀለኞች ላይ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ስራ እና ወንጀለኞቹን አድኖ ህግ ፊት የማቅረብ ስራውንም ችላ ብሎ ቆይቷል ብሏል።
መንግስት የህግ ማስከበር ስራውን ካጠናቀቀ በሗላ የመሰረተ ልማት ጥገና ስራዎችን መስራቱን እና የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ማጠናከሩንም አስታውቋል።
የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱም በበርከታ የትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን መንግስት እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
ይህ ተግባርም በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንዲጎበኝ ተደርጓል ነው ያለው።
የህወሓት ቡድን የጥፋት እና የወንጀል ድርጊቶች በገልተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን ተጠንቶ ግኝቱም ይፋ መደረጉን መግለጫው አንስቷል።
በዚህም መሰረት የጥፋት ቡድኑን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንዳለ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከ27 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን እና ኤርትራውያን ስደተኞችንም አለም አቀፍ መብታቸው ተከብሮ በተመሳሳይ እየኖሩ እንዳለም ነው የገለጸው።
የአውሮፓ ህብረት እንደ ቀደምት መልካም አጋርነቱ ልማትና ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ድጋፉን መቀጠል ይኖርበታል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!