ኢትዮጵያና ህንድ በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ያላቸዉን ትብብር ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያና ህንድ በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ያላቸዉን ትብብር ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደርን በጽ/ቤታቸዉ ተቀብለዉ ባነጋገሩበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነት እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት ለመስራት መክረዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በቀጣይ ከህንድ ሀገር የሚገኙ የትምህርት ዕድሎች ግልጽ ሆነዉ በሁለቱም አገራት እዉቅና በተገቢዉ መመራት እንደሚገባቸዉ ተናግረዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ልምድ ልዉዉጥ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ በኩልም ሁለቱ አገራት በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የትምህርት ዕድልን በሚመለከት በቀጣይ ኢትዮጵያ የሚኖራት ግንኙነት በህንድ አገር ከሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ጋር መሆኑ ቀርቶ ጥራትን መነሻ አድርጎ ከሚመረጡ ዩኒቨርስቲዎች ጋር መሆን እንዳለበትና ይህንን የሚያግዝ ህጋዊ የግንኙነት አግባብ በሚፈጠርበት ሁኔታም ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሽትኪንቶንግ በበኩላቸዉ በህንድ መንግስት በኩል በኢትዮጵያ በተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል በመገንባትና በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነት ላይም መንግስት በሚያስቀምጠዉ አቅጣጫ መነሻ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በምክክሩ ቀደም ሲል በህንድ ዩኒቨርስቲዎች የተማሩ የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ልምዳቸዉን መነሻ በማድረግ በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠቃሚ ሀሳቦችን አንስተዋል።
የኢትዮጵያና ህንድ ግንኙነት በመማር ማስተምርና ሌሎች ዘርፎች 70 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!