የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዴሞክራሲን ማስፈን ግንባር-ቀደም አጀንዳው መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ እና ምጣኔ-ሀብት ክፍል ጋር ተወያየ።
ዴሞክራሲን ማስፈን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንባር-ቀደም አጀንዳ መሆኑን የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውይይቱ አስታውቋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ከአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ እና ምጣኔ-ሀብት ክፍል የፖለቲካ ባለሙያ ኮነር ማክጉአይር ጋር በዴሞክራሲ እና ፓርላማ-ተኮር አጀንዳ ላይ መክረዋል።
ዴሞክራሲ በአንድ የምርጫ ጀምበር የሚወሰን ሳይሆን ቀደም ሲል የሚካሄዱት ነገሮች እና ሂደቶች የዞረ ድምር እና ውጤት መሆኑን የአስገነዘቡት ዶክተር ነገሪ፤ ፓርላማው የፓርላማ ዴሞክራሲን ዕውን በማድረግ እና ሀገራዊ ለውጡን ተከትለው በትክክለኛው መስመር ለመጓዝ ከሚጥሩት የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር በማበር፣ ኢትዮጵያን ወደ እውነተኛው ዴሞክራሲ ለማምጣት እየሠራ መሆኑን ለማክጉአይር እና አብሯቸው ለተገኙት የኤምባሲው ረዳት የፖለቲካ ባለሙያ ለአቶ በላይ ለገሰ አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘውም፤ በየስፍራው ግጭትን የሚቀሰቅሱ የጥላቻ ንግግሮች በሕግ እንዲታገዱ አዋጅ ማውጣቱንም አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ራሱን “ዲጂታል ወያኔ” እያለ የሚጠራው እና አሁን የፓርቲነት ሕልውናው በይፋ የተሰረዘበት የሕወሓት የበይነ-መረብ ክንፍ፤ በብሔሮች መካከል ጠብ እና ግጭትን ሲዘራ እንደነበር ጠቅሰው፣ የተለያዩ የውሸት ስሞችን እየተጠቀሙ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ሁሉ የትሕነግ አንጃ ውጥን እንጂ የሌላ የማንም እንዳልነበሩ ገልጸዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የመከላከያ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ በ1987 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የፓርላማ ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ ያለመ እንደነበር አውስተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ዐቢይ አባል ሆርዶፋ በቀለ በበኩላቸው፤ ፓርላማው ቀደም ሲል ከአሜረካ ኤምባሲ ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ይኼው መልካም የሥራ እና የወዳጅነት ትብብር አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፓርላማው ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ እና የምጣኔ-ሀብት ክፍል የፖለቲካ ባለሙያው ኮነር ማክጉአይር በበኩላቸው፤ መንግስታቸው በፖለቲካው መስክም ይሁን በሌሎች የትብብር ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በተሻለ የትብብር መንፈስ ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!