ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በኢትዮጲያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለፈረንሳይ ኩባንያዎች ማብራሪያ ሰጡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ለፈረንሳይ ኩባንያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር እዮብ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለፈረንሣይ ኩባንያዎች ለማስተዋወቅ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኘው ትልቁ የአሠሪዎችና ኩባንያዎች ማህበር ኤም.ኢ.ዲ.ኢ.ኤፍ ኢንተርናሽናል ተሳትፎ አድርጓል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ስላደረገው ጥረት እና የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ቁልፍ ሚና ለማሳደግ እየተወሰዱ ስላሉ የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያዎች ለፈረንሳይ ኩባንያዎች አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰው፤ በአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ እና ብዝሀነት በማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ዶክተር እዮብ በኢትዮጵያ ከሐምሌ እስከ ታህሳስ 2013 ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንደተመዘገበም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጲያ ትኩረት የምትሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች አግሮ ፕሮሰሲንግ ፣ ቱሪዝም ፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ ማዕድንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ መሠረት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ4ነጥብ7 ቢሊየን ብር በላይ ያፈሰሱ ሲሆን፤ ከ4ሺህ በላይ ቋሚ እና ከ2ሺህ 700 በላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡
ኩባንያዎቹ የተሰማሩት በማኑፋክቸሪንግ ፣ በግብርና ፣ በሪል እስቴት ፣ በሆቴሎች ፣ በቱር ኦፕሬሽንና በሌሎችም መስኮች ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በ19 ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ጀምሮ ረጅምና ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ያላቸው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ውይይቱ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተካሄደ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!