የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አንደኛው የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ ተጀመረ
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ የማደግ እምቅ አቅም እና ተስፋ እንዳላት ጠቅሰው፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራትና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር የሚያደርገው የሰመረ ግንኙነት የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታትና ሀገሪቱን በማሳደግ በኩል አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
አክለውም የምክር ቤት አባላት ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለው ባመኑባቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ይከራከራሉ፣ ህግ ያወጣሉ፣ መንግስትን ይቆጣጠራሉም ነው ያሉት፡፡
በምክር ቤቱ የሚደረጉ ክርክሮች እንዲሁም የሚወጡ ህጎች ደግሞ በጥናት የተለዩ፣ በቂ ማስረጃ ያላቸውና አመክኖአዊ ምክረሃሰብ ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ ተቀባይነት ያላቸውና ለታሰበላቸው ኣላማ ሊውሉ የሚችሉ ውሳኔዎችና ህጎች የማውጣት እድላቸው እንደሚሰፋም አንስተዋል፡፡
በሌላ መልኩ ህግ ፈጻሚው በተነጻጻሪነት የተሻለ የመረጃ እና የእውቀት ምንጮች ያሉት በመሆኑ ምክር ቤቶች ህግ አውጪውን በሚቆጣጠሩበት ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የመረጃ እጥረት መሙላት የሚያስችል አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህን በመረዳትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ሲወጣ የሚያከናውናቸው ተግባራት በመረጃ፣ በእውቀት እና በተቀመረ ልምድ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የዛሬው መድረክም የፓርላሜንታዊ የምርምር መረብ መጠናከር ምክር ቤቱ እያካሄደ ለሚገኘው የሪፎርም /የለውጥ/ አካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥና ፓርላማውም በጥናትና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ በተለይም በሕግ አወጣጥ፤ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ተግባራትን በተገቢው ሁኔታ ለማገዝ እንደሚረዳም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ኔትወርኩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የምርምር ተቋማትን፣ ሃሳብ አመንጪ ተቋማትን፣ የሲቪል ማኅበረሰቡንና የሙያ ማህበራትን ችግር ፈቺ የሆኑ የምርመር ተግባራትን በማካሄድ የሚጠበቅባቸውን ለብሄራዊ ልማት አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ለማስቻል የሚረዳ ነውም ብለዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ የምርምር ኮንፈረንስ በመደበኛነት በየአመቱ የሚከናወኑ ሲሆን ኮንፈረንሱ የሁለት ቀናት ቆይታ የሚኖረውም ይሆናል፡፡
በተስፋዬ ከበደ
ፌስቡክ፡-