በመዲናዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋሽ ባጫ፣ የሁሉም ክፍለ ከተሞች ዋና ስራ አስፈፃሚዎች፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በውይይቱ አቶ ነጋሽ ባጫ በመዲናዋ የሚስተዋሉ እና በጥናት የተለዩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣት ችግሮችን አቅርበዋል፡፡
በዚህም የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ፣ የመንገድ ዳር መብራቶች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት አለመስጠት ፣ የሃይል አቅርቦት ማነስ እና መብዛት፣ የትራንስፎርመር እና የቆጣሪ ጥያቄ መብዛት፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች፣ የውይይት መድረክ ማነስና የክፍያ ማዕከላት አገልግሎት አሠጣጥ ችግር ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ችግሮችም ከህብረተሰቡ በተጨማሪ በተለያዩ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደራቸውን ነው የገለጹት፡፡
በችግሩ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥም የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ፣ የቤቶች ልማት አስተዳደር ፣ የእሳት አደጋ አመራር ኮሚሽን፣ የመንገዶች ባለስልጣን እና የውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በመዲናዋ የመብራት ሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በነዋሪዎች ዘንድ በስፋት ከሚነሱ ቅሬታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ያሉት አቶ ጃንጥራር በተለይም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል አካል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋራ ፎረም ተመስርቷል፡፡
ፎረሙ በመዲናዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት በመስራት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከማስቻሉ በላይ የአገልግሎት አሰጣት ስርዓቱን ለማዘመን እንደሚያስችል ታምኖበታል ፡፡
በመላኩ ገድፍ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!