ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የፍትህ አካላት ጋር የጸረ-ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ንቅናቄ አካሂዷል፡፡
የንቅናቄ መድረኩ ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ኮንትሮባንድ በዘርፈ ብዙ መንገድ ማህበረሰብን የሚጎዳ እና ለሀገር አለመረጋጋት መንስኤ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ የንቅናቄ መድረኮች በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡
ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ በማሳጣት፣ ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ በማስወጣትና ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ በማድረግ ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ያደናቅፋል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ መከላከል ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ በበኩላቸው የኮንትሮባንድ ንግድ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳቶችን በማድረስ ለግጭት መንስኤ በመሆኑ የአገርን ደህንነትን አደጋ ላይ ስለሚጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመቆጣጠር ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
በተሰሩ የመከላከል ስራዎችም በህገወጦች ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት ሊያጣው የነበረን 19.313 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሠመስተዳደር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ህግን በአግባቡ በማስከበር ጥቂቶችን ብቻ ጠቅሞ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ለጉዳት የሚያጋልጥ በመሆኑ በጋራ ልንከላከለው ይገባል ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚነስቴር የህግ ተገዢነት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ጉዳዩ የብዙ አካላትን ትብብር የሚፈልግ በመሆኑ በቅንጅት በመስራት ጉዳቶችን በመቀነስ ለልማት የሚውለው ገቢ እንዲሰበሰብ በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው የሀገር ደህንነትና ጸጥታን ለማስጠበቅ የፌደራል ፖሊስ አባላት እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል እየሰሩ መሆኑን ተናግረው በተለይ ወደ ሀገር በኮንትሮባንድ የሚገቡ እቃዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡