Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጉባ ወረዳ አመራሮች ድርብ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ተገንዝበው እንዲሰሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘውን የጉባ ወረዳ የሚያስተዳድረው አመራር ድርብ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ መስራት አለበት ሲል የተቀናጀ ግብረ ኃይል አሳሰበ።

የጉባ ወረዳ የኢትዮጵያ ትልቁ ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከናወነ ያለበት ስፍራ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሱዳን ጋር የሚያዋስን ወረዳ ሲሆን፤ በመተከል ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር የጉባ ወረዳንም ሰለባ ያደረገ በመሆኑ፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ስጋት ተፈጥሮ እንደነበረ የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በወረዳው ተገኝተው የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ በማስመልከት የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የግብረ ኃይሉ ዋና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ፤ ጉባ ወረዳን መቀየር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት መቀየር ነው ብለዋል።

”ጉባ ላይ የሚከፈል መስዋዕትነት ትልቅ ነው” ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ፤ የጸጥታ ኃይሉ በዚህ ወረዳ ብዙ መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰው፤ አመራሩም ከጸጥታ ኃይሉ በመማር ጉባ ላይ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የወረዳው አገር ሽማግሌዎችና የውይይቱ ተሳታፊዎችም ወደ ስራ የመጡት አመራሮች ‘ደከመኝ ሰለቸኝ’ ሳይሉ ሁሉንም በአንድ አይን በማየት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

የወረዳው ሕዝብም ኢትዮጵያዊያን የሰጡት ትልቅ አደራ በመኖሩ ከአመራሩ ጋር በመተባበር አደራውን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።

የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ቡሴና ረጂብ በበኩላቸው፤ በወረዳው ያጋጠመው የጸጥታ ችግር እየተቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው ያጋጠመው የጸጥታ ችግር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንገት ያስደፋ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት አመራሩ ይሰራልም ብለዋል።

ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ከአገር አልፎ ቀጠናዊ መልክ ያለው መሆኑን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ተናግረዋል።

የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ እስካሁን በዞኑ ጉባን ጨምሮ ዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ወምበራ፣ ቡለንና ድባጤ ወረዳዎች በመገኘት የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ መመልከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.