በሸርቆሌ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ2 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸርቆሌ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሸርቆሌ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል ።
የሸርቆሌ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪ ዋና ሳጅን ሰይፉ ሰሌማን÷ የትራፊክ አደጋው ትናንት ከምሽቱ 12 :30 አካባቢ ከአሶሳ ወደ ሸርቆሌ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ከሸርቆሌ ወደ አሶሳ ይጓዝ ከነበረ ሞተር ሳይክል ጋር በመጋጨቱ የደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአደጋው በሞተር ሳይክሉ ላይ የነበሩ 2 ሰዎች ሕይወት ወድያውኑ ሲያልፍ ከ160 ሺህ ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የትራፊክ አደጋው ሁለቱም አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው እና ተከታታይ መኪኖች ሲያልፉ የአቧራ ግርዶሽ በመከሰቱ መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡
በወረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት በሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ምክንያት የትራፊክ አደጋዎች እየተከሰቱ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ማንኛውም አሽከርካሪ በፍጥነት ከማሸከርከር በመቆጠብ ራሱንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ከትራፊክ አደጋ መታደግ አለበት ማለታቸውን ከቤኒሻንጉል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!