Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ትናንት በደረሱ የእሣት አደጋዎች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት በመዲናዋ በደረሱ ስድስት የእሳት አደጋዎች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማ አስተዳደሩ የእሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ከእሳት ማትረፍ እንደተቻለም ገልጿል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ÷ትናንት በመዲናዋ በስድስት ቦታዎች የእሳት አደጋ ተከስቷል ብለዋል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የቀብር ስፍራ እንዲሁም በወረዳ ሁለት በተለምዶ ሁለት ቁጥር ማዞሪያ በሚባለው ቦታ የእሳት አደጋዎች መከሰታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ደግሞ በመኖሪያ ቤትና በከብቶች በረት፣ እንዲሁም በወረዳ 6 አዲሱ ሚካኤል አካባቢም የእሳት አደጋ መከሰቱን ጠቁመዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በአምስት መኖሪያ ቤቶች፣ ጣፎ መስጊድ አካባቢም እንዲሁ በመኖሪያና የወፍጮ ቤት ላይ የእሳት ቃጠሎዎች መከሰታቸውን አብራርተዋል።
በእነዚህ አደጋዎች በአጠቃላይ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ማትረፍ ተችሏል ነው ያሉት።
በአደጋው አንድ ሰው ላይ ቀላልና 68 የቁም እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አዲሱ ሚካኤል አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ መንስኤው ኤሌክትሪክ መሆኑን የገለጹት አቶ ጉልላት የተቀሩት አካባቢዎች የአደጋ መንስኤ በፖሊስ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
እሳቱን ለመቆጣጠር 221 ሺህ 500 ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ሲውል 150 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
እንዲሁም የፌዴራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊሶች ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ያከናወኑት ተግባር በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.