Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ ክልል ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓት እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል አርሶ አደሩ በግብርና ስራው በስፋት ተሰማርቶ እንዲያመርት መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ የግብርና ግብዓት በማቅረብ ላይ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር የግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ብርሃኔ አርዓያ እንደገለጹት የተፈጠረው ችግር አርሶ አደሩን ጎድቶታል፡፡

በመሆኑም አርሶ አደሩ አሁን ካለበት ተረጂነት እንዲላቀቅና ራሱን እንዲችል በግብርና ስራው ማተኮር እንዳለበት ገልፀው፥ አርሶ አደሩ ተነሳሽነት እንዳለውና የግብርና ግብዓቶች እንዲቀርብ እየጠየቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳዳሩ አርሶ አደሩ የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይገጥመው እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

“እስካሁን ከ66 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የምርጥ ዘር ማሰባሰብ ተችሏል” ያሉት ምክትል ሃላፊው፥ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን ጠቁመዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በ61 ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር የሚደርስ መሆኑንም አመላክተዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተም ለትግራይ ክልል አርሶ አደሮች 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ተገዝቶ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል ነው ያሉት፡፡

300 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ መግባቱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 210 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ክልሉ 500 ሺህ ኩንታል ለማስገባትም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም መንግስት በትግራይ ክልል አርሶ አደሩ ወደ እርሻ ስራው እንዲመለስ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ቢሆንም የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዦች ጫና ለማሳደር እየጣሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም ሳምረ፣ ሚጀታ፣ ሃውዜን፣ እዳጋ ሃሙስ እና አድዋ አካባቢዎች አርሶ አደሩ መሬቱን እንዳያርስ በሬዎችን የማስፈታትና የእርሻ መሳሪያውን የማውደም ተግባር እየተፈጸሙ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የአሸባሪውን ቡድን እኩይ ተግባር በመከላከል የግብርና ስራው እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የፀጥታ ሃይሉ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ማህበረሰቡ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል በዘንድሮው ክረምት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ዕቅድ መያዙን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.