የፋና ቤተሰብ እና አድማጭ “ጀማል ዜና አደም” ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋና ቤተሰብ የሆኑት በቅጽል ስማቸው “ጀማል ዜና አደም” በሚል የሚታወቁት አቶ ጀማል አደም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
አቶ ጀማል አደም ሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም 103.4 ሳይመሰረት በፊት በብሔራዊ ሬዲዮ ከአድማጭነት እስከ ተሳታፊነት ከፋና ጋር ወዳጅነታቸውን አጠናክረው የቆዩና የፋና ቤተሰብ የነበሩ ናቸው፡፡
ሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም ከተመሰረተ በኋላም በቤተሰብነት የቀጠሉ ሲሆን፥ በተለያየ ጊዜ በሲዳምኛ ቋንቋ ዜና ለምን አይነበብም የሚል ቁጭት ስለነበረባቸው በየመድረኩ ዜና በማዘጋጀት ያነቡ ስለነበር ይህንን ቅጽል ስም እንዳገኙ ይነገርላቸዋል፡፡
አቶ ጀማል አደም ዳሬ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ተሳትፎ በተለይም የፋና አሳታፊ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ በሳልና አስታራቂ ሀሳቦችን በመለገስ የሚታወቁ ናቸው፡፡
በሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም በሶስቱም ቋንቋዎች ማለትም በሲዳማ አፎ፣ አፋን ኦሮሞና አማርኛ የሚሰራጩ ፕሮግራሞች ላይ በሳልና አስታራቂ ሀሳቦችን ሲለግሱ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ላይም እርሶ ቢሆኑ በመሳሰሉ ፕሮግራሞች ላይ በቋሚነት በመሳተፍ የፋና ቤተሰብ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ጀማል ዜና አደም የአራት ወንድ ልጆችና የአራት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ በሲዳማ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ በመሰማራት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በተወለዱ በ48 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡
በጌታቸው ሙለታ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!