ወቅታዊው ሁኔታ ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መበራከት ምክንያት እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መበራከት ምክንያት እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ምሁራን ተናግረዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን÷ ሀሰተኛ መረጃዎች በአብዛኛው የራሳቸው ዓላማ ባላቸው አካላት ቢፈበረኩም ዜጎች ደግሞ ባለማወቅ ለጥፋተኞች ሲተባበሩ እንደሚስተዋል አንስተዋል።
በመሆኑም ሆን ተብለው የሚፈበረኩና በዜጎች መካከል ቅራኔን የሚፈጥሩ መረጃዎችን ሳያጣሩ ማሰራጨት ችግሮችን የማባባስ አቅም ስላላቸው መመርመር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
መረጃ ከግለሰቦች እስከ ሀገራት፣ ከምጣኔ ሀብታዊ እስከ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የዘለቀ ጠቀሜታ ባለው በአሁኑ ወቅት እውነተኛ ሀሳቦች ጋር ሀሰተኞቹ እየተዳበሉ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ ይስተዋላልም ነው ያሉት።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህሩ አያሌው ደጀን÷ የመረጃ በሀሰት መበረዝ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል የሚል ሀሳብን ያቀርባሉ፡፡
እነዚህ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሊበዙ እንደሚችሉም ነው የሚናገሩት፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚያደርጉት ደግሞ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከ ምርጫ ያሉ ሰሞነኛ ጉዳዮችን ናቸው ብለዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ እንግዳ ወርቅ ታደሰ በበኩላቸው÷ ሀሰተኛ መረጃዎች ሆን ተብሎ ለራስ ፍላጎት ወይም ከትክክለኛ ምንጭ ያልሆነ መረጃን በማሰራጨት እንደሚስፋፋ ተናግረዋል።
ሆኖም እንደቀልድ የተሰራጨው መረጃ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል፣ የዜጎችን የእርስ በርስ ግንኙነት ሊያሻክር ይችላልም ነው ያሉት፡፡
እንደምሁራኑ ገለፃ ችግሩ አሳሳቢነቱ የጎላ ስለሆነ ለመፍትሄው መንግስት የመረጃ ስርዓቱን በማቀላጠፍ፣ መገናኛ ብዙሃንም ለእውነት በመወገን መስራት አለባቸው፡፡
ማህበረሰቡ ደግሞ ነገሮችን መመርመርና ፍሬውን ከገለባው እውነቱን ከሀሰቱ መለየት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ስራ ላይ ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሀሰተኛ መረጃ ቁጥጥር ዘዴያቸውን ማጥበቅ እንደሚጠበቅባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአፈወርቅ እያዩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!