በ800 ሚሊየን ብር ለሚገነባው የሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልህቀት ማዕከል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ800 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው የሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልህቀት ማዕከል የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ሀገር የሚለወጠው በተማረና በሰለጠነ የሰው ሀይል መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የጎላ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።
በ800 ሚሊየን ብር የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑንና ለተለያየ ዘርፍ የሚውል በርካታ ክፍሎች ያሉት እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሙሉ ነጋ የልህቀት ማዕከሉ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በከተማዋ ትልልቅ ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አስተዳደሩ ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡
ከንቲባው የፕሮጀክቱን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመግለጽ ለፍጻሜው ከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለታቸውን ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!