የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም የመሰናዶ ትምህርት ፈተና ወስደው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል፡፡
በተያዘው የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች ብዛትም 3 ሺህ 559 መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ 1ሺህ 500 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው እየገቡ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ተማሪዎች ምንም አይነት መንገላታትና ችግር እንዳይገጥማቸው አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ተማሪዎችን ድሬደዋ ከገቡበት ሰዓት አንስቶ አቀባበል በማድረግ እስከ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ድረስ በማምጣት ምዝገባ እንዲፈጽሙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ሰኔ 28 ፣29 እና 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የተፈጥሮ ሳይንስና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች መረጃን ወደ በይነ መረብ የማስገባቱ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
ሐምሌ 01 ና 02 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ኦረንቴሽን የሚሰጥ ሲሆን÷ በዚህም ተማሪዎች በዩኒቨርሲተው በሚኖራቸው ቆይታ ዩኒቨርሲቲው ስላወጣቸው ደንብና መመሪያዎች ገለፃና ማብራሪያ ይሰጣቸዋል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም ተማሪዎች ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ኮቪድ 19 አስመልክቶ በጤና ባለሞያዎች ትምህርት እንደሚሰጣቸውመናገራቸውን ከዩኒቨርሰቲው ዓለም አቀፍ እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሐምሌ 03 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እምደሚጀመር የገለፁት ዶክተር መገርሳ÷ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ባስቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!