Fana: At a Speed of Life!

ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል አገራት የተውጣጡ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል አገራት የተውጣጡ ወጣቶች አዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ።
በምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አዘጋጅነት የአባል አገራቱ ወጣቶች በሰላም ላይ ያተኮረ ልምድ ልውውጥና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ወጣቶቹ በትናንትናው እለት በቀጣናው ሰላምና ወቅታዊ ሁኔታ የወጣቶች ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሃ ግብር መዝጊያ ስነ ስርዓቱ ወጣቶቹ በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ የተከሉ ሲሆን፥ የተጠባባቂ ሃይሉን ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።
የተጠባባቂ ሃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው፥ ”የአረንጓዴ አሻራ በማሳረፋችን ኮርተናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም የተጠባባቂ ሃይሉ አባል አገራት ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ አካል እንዲሆኑ በመፍቀዱ ይመሰገናል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ ተግባር በአባል አገራቱ እንዲስፋፋ ጥረታቸውን እንደሚያጠናክሩም ነው የገለጹት።
የግብርና ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለግብርና ዘርፍ ካለው ጠቀሜታ አንጻር እየተሰራ ያለው ስራ የሚደገፍ ነው ብለዋል።
ችግኝ የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የቤተሰብ የሀይል ፍላጎት ማሟያ ሆኖም የሚያገለግል በመሆኑ የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።
በዚህ ዓመትም ኢትዮጵያ 6 ቢሊየን ችግኝ በአገር ውስጥ ለመትከል ማቀዷንና 1ቢሊየን ደግሞ ለጎረቤት አገራት ማዘጋጀቷን ጠቅሰዋል።
እቅዱ እንዲሳካ ወጣቶች የነገ ሕይወታቸው የተሻለ እንዲሆን ለዚህ በጎ ተግባር ሊረባረቡ ይገባልም ብለዋል።
የምሰራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል አባል አገራት ወጣቶችም ኢትዮጵያ መጥተው ችግኝ በመትከላቸው ሊመሰገኑ ይገባልም ነው ያሉት።
የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ህይወት ሀይሉ፤ ችግኝ ተካላ የድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃ አገልግሎት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት ተግባር ጠቃሚና የጋራ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር ትስስርም የሚያበረታ በመሆኑ ሊለመድ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶችም በሌሎች የቀጣናው አገራት ተዘዋውረው ችግኝ መትከልና ለሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ እቅድ መኖሩን ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል 10 አገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን፥ በሰላምና ደህንነት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ነው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.