Fana: At a Speed of Life!

የህዝብ ድምፅ የበላይነትን እንደሚያከብሩ የደቡብ ክልል ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ድምፅ የበላይነትን እንደሚያከብሩ የደቡብ ክልል ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
ለምርጫው ሰላማዊነት የህዝቡ የነቃና ሰፊ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንም ፓርቲዎች ባወጡት ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርገዋል።
በደቡብ ክልል በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ብልጽግናን ጨምሮ 21 ፓርቲዎች እጩዎችን አቅርበው በምርጫው ተሳትፈዋል።
የጋራ ምክር ቤት አቋቁመው በምርጫው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ ሲሰሩ የቆዩት እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዛሬው እለት በሀዋሳ ውይይት አካሂደዋል።
ፓርቲዎች በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የህዝብ ድምፅ የበላይነትን እናከብራለን ሲሉ አሳውቀዋል።
በክልሉ ምርጫ በተካሄደባቸው 88 የምርጫ ክልሎች ተፎካካሪ የነበሩት እነዚህ 21 ፓርቲዎች ባወጡት ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ÷ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንደነበረ በመግለጽ ለዚህም ባለድርሻ አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባ አንስተዋል ።
በተለይም ለመራጩ ህዝብ ታላቅ አክብሮትና ምስጋና እናቀርባለን ሲሉ አሳውቀዋል።
ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ በምርጫ ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ ሁልጊዜም የሚኖር በመሆኑ በህዝብ ድምፅ የበላይነት እናምናለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሁሉም ፓርቲዎች ፣አባላትና ደጋፊዎች ውጤቱን በጸጋ እንዲቀበሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከደቡበ ክልለ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለጸጥታና ለፍትህ አካላት፣ለመገናኛ ብዙሃን፣ለክልሉ መንግስትና ምክር ቤት፣ለምርጫ ቦርድና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም መንግስት ለብሄራዊ መግባባትና ሀገራዊ ጥቅም እንዲሰራ የጠየቁ ሲሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ባለፈ በልማታዊ ስራዎችም በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል ።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.