በመዲናዋ በሀሰተኛ ብር ሲገበያዩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 25 ሺህ ሃሰተኛ ብር እና 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል ባለ 200 የብር ኖቱን በባለ ቀለም ማተሚያ ማሽን ስታባዛ የነበረች ግለሰብ ትገኝበታለች ተብሏል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ግራር ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ ወደ ሱቅ በመሄድ የሞባይል ካርድ ለመግዛት ባለ 200 የብር ኖት እንደሰጠ እና ባለሱቆቹም የተቀበሉትን ብር ተጠራጥረው ወዲያውኑ ለፖሊስ በማሳወቃቸው ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎታል፡፡
ግለሰቡ ለባለ ሱቁ የሰጠው ገንዘብ ሃሰተኛ ስለመሆኑ መረጋገጡን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ÷ በወቅቱም ኪሱ ሲፈተሽ ተጨማሪ 3ሺህ 800 ሃሰተኛ ብር መገኘቱን ገልጿል፡፡
የሃሰተኛ ገንዘቡን ምንጭ ለማወቅ ፖሊስ ባደረገው እንቅስቃሴ ተጨማሪ 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመላክቷል፡፡
ከእነዚህም መካከል በአንደኛው ግለሰብ ኪስ 1ሺህ 200 መቶ፣ በሌላኛው ግለሰብ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 20 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት ተገኝቷል፡፡
ሶስተኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ አንዱን ባለ 200 ሃሰተኛ የብር ኖት 15 ብር እየተከፈላት በባለ ቀለም ማተሚያ ማሽን ለሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ስታባዛ የነበረች መሆኗን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ 4 ተጠርጣሪዎች እና 25 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት እንዲሁም ሲገለገሉባቸው የነበሩ ፕሪንተር ማሽን እና ኮምፒውተር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ግብይት በሚያከናውንበት ወቅት መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ትኩረት እና ጥንቃቄ ማድረግ እና ለፀጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!