Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዳሴ ግድቡ መገኛ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ልዩ ትርጉም ተሰጥቶት ይከናወናል- አቶ አሻድሊ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዳሴ ግድቡ መገኛ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ልዩ ትርጉም ተሰጥቶት እንደሚከናወን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ፣ የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በተገኙበት በአሶሳ ወረዳ መንገሌ 38 ቀበሌ ተጀምሯል።
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶ/ር ግርማ አመንቴ እና የአማራ ክልል መንግስት ተወካይና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መለሰ መኮንን እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የሴክተር መ/ቤት ሠራተኞች፣ የበጎ አድራጊ ወጣቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
አቶ አሻድሊ ሃሰን “ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል በተያዘው 3ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 72 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የችግኝ ተከላ ዘመቻው በክልሉ ዛሬ በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ክልሉ የሕዳሴ ግድቡ መገኛ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ልዩ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር እና የአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ሁለት ድሎችን ማስመዝገቧን ጠቁመው፣ 2ኛው ዙር የውኃ ሙሌት እየተከናወነ ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቱ ደምጿን ከፍ አድርጋ ፍትሃዊ የአባይ እናት መሆኗን ለጸጥታው ምክርቤት ያስመሰከረችበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ ችግኞችን በዘመቻ ከመትከል በተጨማሪ ባህል ሊያደርግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ÷ የተተከሉትን ችግኞች መንከባከብ እና ዛፎች እንዳይቆረጡ በማድረግ ሀገራችንን ለዜጎቿ የምትመች ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶ/ር ግርማ አመንቴም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተተከሉ ችግኞች ልዩ ትርጉም ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ተወካይና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መለሰ መኮንን÷ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው፣ አሁን እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ለኢትዮጵያ ድርብ ድል በተገኘበት ወቅት በመሆኑ የተለየ ስሜትና ትርጉም ያለው ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የሚተከሉ ችግኞች ሲዘጋጁ ጀምሮ ጥራታቸውን እንዲጠብቁ ከማስቻል ባለፈ በአግባቡ ተተክለው እና እንክብካቤ ተደርጎላቸው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.