ባንኩ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ለሚገነባው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የ83 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ብድር አጸደቀ
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ለሚገነባው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የ83 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ብድር ማጽደቁን አስታወቀ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር አካባቢ ለሚገነባው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የሚውሉ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ሁለት ብድሮችን ማጽደቁን ይፋ አድርጓል፡፡
ባንኩ ካጸደቃቸው ሁለት ብድሮች መካከል 69 ነጥብ 65 ሚሊየን ዶላሩ ለኢትዮጵያ እንዲሁም 13 ነጥብ 93 ሚሊየን ዶላሩ ለጅቡቲ የሚሰጥ መሆኑን ኢነርጂ ሚክስ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
የብድሩ ምንጭ የአፍሪካ የልማት ፈንድ ሲሆን÷ በረዥም ጊዜ ከሚከፈል የብድር ማዕቀፍ እንደተገኘም ባንኩ አስታውቋል፡፡
ብድሩ የተሰጠው ለሁለተኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት የሚውል ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የመስመር እንዲሁም 170 ኪሎ ሜትር የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ጨምሮ ንዑስ የሀይል ተሸካሚዎችን ለመገንባት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ይህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በሀይል በማስተሳሰር የአካባቢውን መሰረተ-ልማት በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እንደሚያመጣ የባንኩ የሀይል ስርዓት ግንባታ ዳይሬክተር ባቺ ባልዴህ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በሁለቱም ሀገራት እየተስፋፉ በመጡት ልማቶች ማለትም የምስራቁ ኢትዮጵያ አካባቢ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ከጅቡቲ ተነስቶ ኢትዮጵያ የሚደርሰው የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ እንዲገናኝ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ ይህን ሁለተኛ ዙር የብድር ድጋፍ ማድረግ የቻለው በፈረንጆቹ በ2004 ለመጀመሪያው ዙር የሀይል መስመር ዝርጋታ የሰጠው በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር አጥጋቢ ውጤት በማስገኘቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በዚህም ጅቡቲ ከውሃ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማምረት ልትገነባ የምትችለውን የሀይል ማመንጫ ግድብ ፍላጎት ወደ 16 በመቶ እንዲቀንስ በማድረጉ÷ በጅቡቲ 65 በመቶ የሀይል አቅርቦትን ለደንበኞች እንዲደርስ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ኢትዮጵያ በወቅቱ ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ 275 ሚሊየን ዶላር ገቢ መሰብሰብ መቻሏን በማሳያነት አንስቷል፡፡
ይህ ሁለተኛው ዙር የሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የምታገኘው ገቢ የሚያሳድግ ሲሆን÷ ጅቡቲም አንድ ኪሎ ዋት በሰዓት ከ10 የአሜሪካ ዶላር ሳንቲም በታች በሆነ ዋጋ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ሀይል እንድታገኝ የሚያስችላት ነው።
ለሀገሪቱም ገበያ ምቹ ሁኔታ ለወጣት ዜጎቿ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችላት እንዲሁም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የበካይ ጋዝ ልቀት እንደሚቀንስ መረጃው ማስታወሱን ኢዜአ ዘግቧል።