Fana: At a Speed of Life!

ከ165 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ምርቶች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 26፣ 2013 ( ኤፍ ቢ ሲ)ከ165 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የኮትሮባንድ እና በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችቶ የተገኙ የተለያዩ ምርቶች መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የ2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች እና ከክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን ጋር በዝርዝር ገምግሟል፡፡

በበጀት ዓመቱም 165 ሚሊየን 16ሺህ 389 ብር የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ እና በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችተው የተገኙ ልዩ ልዩ ምርቶችን በመውረስ ለመንግስት ገቢ መደረጉን የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ገልጸዋል፡፡

በንግድ ቁጥጥር ስራ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ 325ሺህ የንግድ ድርጅቶች የንግድ ህግን ተከትለው እየሠሩ መሆናቸውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ከህግ ወጪ ሲሰሩ የተገኙ 54ንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ እስከማገድ ድረስ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተሳሳተ እና ከልኬት በታች ሲለካባቸው የነበሩ 1ሺህ 459 የልኬት መሳሪያዎች እና ሚዛኖች በቁጥጥር ስር ውለው እንዲወገዱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በ2013 በተለያዩ ንግድ መስኮች ለሚሠማሩ 112ሺህ 941 አዳዲስ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ እንደተሰጠ አቶ አብዱልፈታ መግለጻቸውን ከከተማው ፕረስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በ2014 በጀት ዓመትም የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.