Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን የሰላም ልዑካን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን የሰላም ልዑካን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ዘጠኝ አባላት ያሉት እና ከ13 የሲቪክ ተቋማት የተወከሉ ትውልኢትዮጵያዊያንን ያካተተው በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን የሰላም ልዑኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውሮ ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል፡፡
 
የሀገራቸውን መልካም ገጽታ ለመገንባት በተለይ በሚኖሩባቸው የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በቂ እና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አባላቱ አብራርተዋል።
 
ኢትዮጵያን መውደድ በተግባር መታየት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡት ፕሬዘዳንት ሣህለወርቅ÷የኢትዮጵያ ጉዳይ ለተወሰኑ ብቻ ያልተከለለ በመሆኑ ያገባኛል ብለው እያከናወኑ ላለው ተግባር አመስግነዋል።
 
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ሁላችንም የተለያየን በመሆናችን በቤተሰብ ደረጃ እንደምናደርገው ሁሉ ሰንሰለቱን ሳንበጥስ ተቻችሎ አብሮ መኖር፣ አንዳችን ለአንዳችን የሠላም ምንጭ እንጂ የጥላቻና የስቃይ ምንጭ ላለመሆን ሁላችንም በርትተን መሥራት አለብን ብለዋል፡፡
 
ልዑካኑ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመጎብኘት ባለፈ የተለያዩ ድጋፍችን ማድረጋቸውንም ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.