ዲጂታል ጅማ የተሰኘ የልህቀት ማዕከል በጅማ ዩኒቨርስቲ ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡና ምርት እና የግብይት ስርዓት፣ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ገበያ ማስገባት እና ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ማመቻቸት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዲጂታል ጅማ የተሰኘ የልህቀት ማዕከል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቋቋመ፡፡
የልህቀት ማዕከሉ በሀገሪቱ የሚገኙ መሰል ተቋማት የአተገባበር ክህሎትና ልምድ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ወርክሾፕ በዩኒቨርስቲው ግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡
ወርክሾፑ በኦንላይን ገንዘብ ልውውጥ ግንዛቤ መፍጠር፣ ባለድርሻ አካላትን መለየት፣ የሙከራ ፕሮጀክት ትግበራ ቦታ ልየታ እና የፕሮጀክት ትግበራ ዘዴዎችን መለየትን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ግብርናን በቴክኖሎጂ ማዘመን እና የተመራቂዎችን የመቀጠር እድል ለማጎልበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ አፍሮ ቫሊ እና ጅማ ዞን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል።
የፈጠራ ባለሙያዎችን በኦንላይን የገንዘብ ልውውጥ ዘዴ ገበያ እንዲፈጠርላቸዉ ማድረግ እና የተማሪዎችን የመቅጠር አቅም ለማሳደግ የስራ ፈጠራን ማበረታታት ላይ ያተኩረ ውይይትም ተደርጓል።
ዲጂታል ጅማ የልህቀት ማዕከል መመስረት በቡና ምርትና የገበያ ትስስር ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ውስብስብ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ፈጣንና ቀልጣፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የፈጠራ ባለቤቶችን ስራዎች ወደ ገበያ በማስገባት የአገልግሎት ሰጪ እና ተጠቃሚ ግንኙነትን ለማጎልበት እና የተመራቂ ተማሪዎችን የመቀጠር እድሎችን ለማስፋፋት ቀጣሪ ተቋማትን እና ተማሪዎችን የሚያስተሳስር ስርዓት ለመፍጠር እንደሚጠቅም ተነግሯል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!