ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከማሸነፍ እንጂ ከመሸነፍ ጋር ተጠርቶ አያውቅም-ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲሱ ዓመት ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና የምንገላገልበት፣ አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት፣ ከደረሰብን ፈተና የምናገግምበትና ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ብልጽግና የምናዞርበት እንደሚሆን እምነቴ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ዓመት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናበት፣ ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶቻችን የሚጎለብቱበት፣ የጀመርነው ሪፎርም መልክ የሚይዝበት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋም አመልክተዋል።
ምንም ያልተጻፈበት አዲሱ ዓመት 2014 ዓ.ም. ሁለት ነገሮችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ እነሱም በባዶው ገጽ ላይ የሚጽፍ ጀግና እና የሚጻፍበት ታሪክ መሆናቸውን ነው ያወሱት።
አሁን ያለው ቁልፉ ጥያቄ በዚህ ለሁሉም ባዶ ሆኖ በቀረበው አዲሱ የዘመን መጽሐፍ ላይ እኛው ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ዕጣ ፈንታ እንጽፋለን? ወይስ ሌሎች እንዲጽፉልን አሳልፈን መጽሐፉን እንሰጣለን? የሚል ነው ብለዋል።
የዘመን መጽሐፍን የፈጠርን እኛው ኢትዮጵያውያን በዘመን መጽሐፉ ላይ በራሳችን መንገድ የራሳችን ዕጣ ፈንታ በእጆቻችን ለማሳረፍ የሚያቅተን ነገር የለም ሲሉም አስገንዝበዋል።
ዕንቅፋቶቻችን እየተወገዱ ነው፤ ወደረኞቻችን ሁሉ ድል እየሆኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘመኑ የኢትዮጵያ ፤ አዲሱ ዓመት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአዲሱ የዘመን መጽሐፍ ላይ አዲሱን የብልጽግና ጉዞዋን፤ ድሏንና አሸናፊነቷን፣ ክብሯንና ታላቅነቷን ትጽፍበታለች ብለዋል።