በአጋሮ ከተማ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 25 ሚሊየን ብር የሚገመት ስራ ተከናውኗል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 25 ሚሊየን ብር የሚገመት ስራ መከናወኑን የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ነሲብ ያሲን አስታውቀዋል፡፡
በከተማዋ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመዝጊያ መርሃግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰሩ 41 አዳዲስ ቤቶች ለአቅመ ደካማ ወገኖች ተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም 37 ያረጁ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ተደርጓል ተብሏል፡፡
ቤት ያገኙ እናቶች በበኩላቸው ከዚህ በፊት በቤት ኪራይ ሲደርስባቸው የነበረውን እንግልት አስታውሰው÷ ለተደረገላቸው እርዳታና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአጋሮ ከተማ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 150 ዩኒት ደም መሰብሰቡም ተጠቁሟል፡፡
በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም 518 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ነሲብ ያሲን ገልፀዋል፡፡
ለአቅመ ደካሞች የሚውል 700 ኩንታል የምግብ እህል መሰብሰቡንም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 25 ሚሊየን ብር የሚገመት የማህበረሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰራቱን ከንቲባው አብራርተዋል፡፡
በዛሬው መርሃ ግብርም 1600 ጫማ እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ለ350 ተማሪዎች በድጋፍ ተበርክቷል።
እንደ ጅማ ዞን በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 847 ሚሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱላኪም ሙሉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም 3007 ቤቶች ተሰርተው ለአቅመ ደካሞች ተላልፈው መሰጠታቸውን ገልፀዋል፡፡
በወርቃአፈራሁ ያለው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!