የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 100ኛ መደበኛ ስብሰባው በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች ማስተላለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።
ጽ/ቤቱ እንዳስታወቀው ውይይቱ የተካሄድው በፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ፥ የመንግሥት ሠራተኞች እና የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ጡረታን ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ ዐዋጆች እንዲሁም በማዕድን ስምምነቶች እና የተሐድሶ ሕክምና አገልግሎትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው።
ከነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ያለው የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ጥቂት አንቀጾች ግልጽነት የሚጎድላቸውና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫናን ያሳደሩ ሆነው በመገኘታቸው ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በቀረበለት ረቂቅ የማሻሻያ ደንብ ላይ ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወስኗል፡፡
በጡረታ አገልግሎት ዐቅድ ለሚሸፈኑ ባለመብቶች ፈጣን፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታ ለማሳደግ እንዲሁም ግልጽ የፈንድ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት በስራ ላይ የነበሩትን አዋጆች ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጆቹ ላይ እንዲሁ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል፡፡
በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ላይ ምክር ቤቱ ባካሄደው ውይይት የኢንቨስትመንቶቹ መተግበር ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኙ፣ ከ1ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተመልክቷል።
ኢንቨስትመንቶቹ በሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ የኮርፖሬት ማህበራዊ ኃላፊነት መርህ የሚያገለግሉ እና የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በስምምነቶቹ መካተታቸውን በማረጋገጥ ግብዓቶችን በማከል ስምምነቶቹ እንዲፈረሙና ወደ ስራ እንዲገባ ምክር ቤቱ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ የተወያየባቸው ጉዳዮችና ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የፌደራል የገቢ ግብር ደንብን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ከነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን የኢትዮጵያ የገቢ ግብር ስርአት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ መምራት የሚያስችል እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
ሆኖም ጥቂት የደንቡ አንቀጾች ግልጽነት የሚጎድላቸውና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫናን ያሳደሩ ሆነው በመገኘታቸው ማሻሻያው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ የማሻሻያ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ስለመንግስት አገልግሎት ጡረታ እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ጡረታን ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡
መንግስት የዜጎችን ከአገሪቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም እያካሄደ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ይገኛል፡፡
በጡረታ አገልግሎት ዐቅድ ለሚሸፈኑ ባለመብቶች ፈጣን፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታ ለማሳደግ እንዲሁም ግልጽ የፈንድ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት በስራ ላይ የነበሩትን አዋጆች ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጆቹ ተዘጋጅተው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች በማከል ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ላይ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ ባዋቀረው የህግ፣ የቴክኒክና የኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ኮሚቴ የኢንቨስትመንቶቹ አዋጭነት፣ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ጠቀሜታ እና በኩባንያዎቹ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተአማኒነት በዝርዝር ተገምግሞ ስምምነቶቹ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡
ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንቶቹ መተግበር ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኙ፣ ከ1ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ፤ ኢንቨስትመንቶቹ በሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ የኮርፖሬት ሶሻል ሪስፖንሲቢሊቲ መርህ የሚያገለግሉ እና የአካባቢውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በስምምነቶቹ መካተታቸውን በማረጋገጥ ጥቂት ግብዓቶችን በማከል ስምምነቶቹ እንዲፈረሙና ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!