የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሃግብር አካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሃግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲንን ጨምሮ የፓርቲውከፍተኛ አመራሮችና እጩ ተወዳዳሪዎች በተገኙበት አካሂዷል።
በወቅቱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፥በክልሉ ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ ተጠናቋል ብለዋል።
በተለይም ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አንፃርም በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልም ምርጫው የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ድጋፉን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ዘንድሮ የሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
“ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች እኩልና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ያስተናግዳል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፓርቲው በወንድማማችነት፣ በመተባበርና መቻቻል ያምናልም ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ያቀረባቸው እጩዎች ወጣቶችና ሴቶች ስለመሆናቸው ጠቁመው፥ ይህም ፓርቲው ለወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት መረጋገጥም ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያመላክታል ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በበኩላቸው ፥ፓርቲው የምርጫ ቦርድን ህግና መመሪያ ባከበረ መልኩ የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳና የመራጮች ምዝገባ ሲያካሄድ ቆይቷል።
የክልሉ ህዝብም በነቂስ በመውጣት ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ መውሰዱን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ህዝቡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ ላይም እጩዎች የማስተዋወቅ መርሃግብር ተካሂዷል።
በመድረኩም በክልሉ ከገጠርና ከተማ የተወጣጡ የፓርቲው አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!




+4
0
People Reached
15
Engagements
Boost Post
15