የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው 416 ሰንጋዎችን ድጋፍ አደረገ።
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙቀት ታረቀኝ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ፥ መከላከያን መደገፍ አገርን ማሳደግ ነው፣ ሰላምን ማስፈን ነው፣ የአገርን ብልጽግና እውን ማድረግ ነው፣ ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን እውነተኛ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የህግ ማስከበር ዘመቻው እስኪጠናቅቅ ድረስ ህዝቡ አብሮ ለመታገልም፣ ባለው አቅም የመከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍም ዝግጁ በመሆኑ ድጋፉን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አቶ ሙቀት ተናግረዋል፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ህብረተሰብ በማስተባበር እስከካሁን ለመከላከያ ሰራዊት በመጀመሪያው ዙር 123 ሚሊዩን ብር፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 609 በሬዎችን፣ አንድ ሺህ 634 በጎችንና የአንድ ሚሊየን ብር የሚገመት የሥንቅ ድጋፍ ከህብረሰቡ በማሰባሰብ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያን በመበተን ወደ ትናንሽ መንደር ለመቀየር ካፈጣጠሩ ጀምሮ ሲታገል የነበረው ጠላት ያለመው እንዳይሳካ የሚደረገውን ዘመቻ እንደግፋለን፣ የበለጠ ተጠናክሮ ህግ የማስከበር ስራ እንዲሰራ፣ አገር ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀበሩ የማድረግ ትግሉን እንደግፋለን፡፡
ተመልሶ የማይተካ ሕይወቱን መስዋዕት እያደረገ የህዝቡን ህልውና እንዲጠበቅ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር እየታገለ ላለው የመከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ ሚኒስቴር የህብረት ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ፋይናንስ ስራ አመራር ዳይሬክተር ብርጋዴል ጀነራል አስረስ አያሌው ሰራዊትን በመወከል ባደረጉት ንግግር ፥ ከአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተማዎች ከተለገሱት ሰንጋዎች ከፍተኛው ቁጥር የሚይዘው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ መሆኑን ኢፕድ ዘግቧል።
ለአንድነታችንና ለሉአላዊነታችን የሚገባውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ህዝብ በደም ልገሳ፣ በገንዘብ፣ በሰው ሃይል፣ በስንቅና በሞራል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!