በክልሉ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ክርክሮችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል-የሀረሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት
አዲስ አበባ፣መስከረም 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ክርክሮችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ማሒር አብዱሰመድ ፥በእረፍት ምክንያት በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩ ፍርድ ቤቶች ከዛሬ መስከረም 18/ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የክልሉ ፍርድ ቤቶችና ችሎቶች ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ቀደም ሲልም ዳኞች በእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው በመልካም ፍቃድ ላይ በተመሰረተ መልኩ ለምርመራ፣ ለብይን እና ለውሳኔ የተቀጠሩ በርካታ መዝገቦች እልባት እንዲያገኙ የማድረግ እና ለረዥም ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ የመዛግብት ክምችትን በከፍተኛ ሁኔታ ማጥራት ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት ባለፉት ዓመታት የተጀመረው የማሻሻያ ስራዎች በማጠናከር ስራዎችን በታማኝነት ፣ በቅልጥፍናና በጥራት እንዲሁም በተጠያቂነት መንፈስ ለመወጣት እና ህብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን አማኔታ እንዲጎለብት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ ከሚካሄደው ስድስተኛውን ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተያይዞ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚቀርቡ ክርክሮች ለማስተናገድ የክልሉ ፍርድ ቤቶች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የክልሉ መንግስት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡ ህግና ስርዓትን ባከበረ መልኩ በመንቀሳቀስ ማናቸውንም ቅሬታም ሆነ አቤቱታዎች በህጉ መሰረት መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ለህግ የበላይነት ተገዥ እንዲሆኑና ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!