የለጋንቦ ወረዳን ጨምሮ የጊንባና የ አቀስታ ከተሞች በደላንታ ግንባር በመገኘት ለሰራዊቱ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጊምባ እና የአቀስታ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የለጋንቦ ወረዳ በደላንታ ግንባር በመገኘት ከ7 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የቁም እንስሳት ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ከእዚህ ውስጥ የጊምባ ከተማ አስተዳደር 325 ሺህ ብር ግምት ያላቸው በጎችን አበርክቷል።
የጊምባ ከተማ አስተደደር ከንቲባ አንዋር እሸቴ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን ለማሳየት በሁሉም መስክ እየተረባረበ ነው፤ ድጋፉም የእዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ እየተሳተፈበት ያለው የህልውና ዘመቻ አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ ነዉ ብለዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ደግሞ ህዝቡ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ በአይነት እና በገንዘብ ብቻ የሚገለፅ አይደለም ልጆቹንም መርቆ ወደ መከላከያ እየላከ ነው ብለዋል ጀነራሉ፡፡
ጁንታው በአሁኑ ሰአት ቅስሙ ተሰባብሮ እየተፍረከረከ ስለሆነ÷ መድረሻ ያጣ ውሻ የሚረግጠውን አያውቀውምና ማህበረሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት አካባቢውን ነቅቶ ይጠብቅ ሲሉ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ መልእክት አስተላልፈዋል።
በእሸቱ ወ/ሚካኤል ሐብታሙ ተ/ስላሴ