መምሪያው በአንደኛው ሩብ ዓመት ከ280 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት10፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ)የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሶስት ወራት አፈፃፀም መደበኛ ከሆኑ የገቢ ምንጮችና ከአገልግሎት ዘርፍ 280 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ባለሙያ አቶ ንጉሴ አጎናፈር እንደገለፁት÷ በዞኑ ስር ከሚገኙት 22 ወረዳና ዘጠኝ ከተማ አስተዳደሮች 1ነጥብ 59 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከዚህ ውስጥም በአንደኛው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ከመደበኛና ከአገልግሎት ገቢ 280 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
መምሪያው ባለፉት 3 ወራት ሊሰበስብ ካቀደው 280 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ውስጥ ከመደበኛ ገቢ 269 ነጥብ 2 ሚሊየን እና ከከተማ አገልግሎት 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን÷ ገቢው ከባለፈው 2013 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር 40 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡
ለተሰበሰበው ገቢ አስተዋፅኦ ካበረከቱ ጉዳዮች ውስጥ የ2014 ዓ.ም የገቢ እቅድ ውጤት ለመፈጸም በዞን ደረጃ ከወረዳዎችና ከተሞች የገቢ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ወደ ስራ መገባቱና የደረጃ “ሀ” “ለ” እና “ሐ” የንግድ ስራ ግብር ከፋዮች በወቅቱ ክፍያ መፈፀማቸው በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን የተቋሙ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም የአጋር አካላት ጥረት የታከለበት መሆኑን አቶ ንጉሴ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ወራትም ቀሪ እቅዶችን ለማሳካት ጥረት የሚሹ ገቢዎችን ለይቶ ለመስራት የግብር ከፋዮች ደረሰኝ አሰጣጥ ማሻሻል እንዲሁም አጋርና ባለድርሻ አካላት የገቢ ስራዎችን እንዲደግፉ በማድረግ ለታክስ ህግ መከበር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም መምሪያው መግለፁን ከዞኑ ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!