Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስር እየተከናወነ በማስመሰል የሚሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው-ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስር እየተከናወነ በማስመሰል የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀና መሰረተ-ቢስ ውንጀላ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ እንዳሉት÷ በመዲናዋ ጥቆማን መሰረት ተደርጎ በተከናወነ ፍተሻ በርካታ የሀሰተኛ ሰነዶች እና የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል።
 
በተለያዩ አካባቢዎችም የጦር መሳሪያዎችና ተተኳሽ ጥይቶች በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ተጥለው እየተገኙ እንደሆነም ገልጸዋል።
 
የህወሃትና ሸኔ አሸባሪ ቡድኖችን ዓላማ ለማስፈጸም ራሳቸውን ቀይረው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች ከያዟቸው የሬድዮ መገናኛ እና የሳተላይት ስልኮች ጋር በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።
 
በዚህም የአሸባሪ ቡድኖቹ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምን ለማወክ ይዘውት የነበረው እቅድ ማክሸፍ መቻሉን አውስተዋል፡፡
 
በዚህ ሁሉ ሂደት የመዲናዋ ነዋሪዎች ያደረጉት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
 
አሸባሪው ህወሃት ህዝብን ለማሸበር የሚጠቀምበት ዋነኛው ዘዴ ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት መሆኑን ገልጸው፤ ከሰሞኑም በመዲናዋ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስር እየተከናወነ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ይገኛል ነው ያለት፡፡
 
ፖሊስ ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ የአሸባሪ ቡድኖችን ዓላማ ለማስፈጸም እንደሚንቀሳቀሱ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ለይቶ በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ውንጀላው መሰረተ ቢስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ህብረተሰቡ ህገ-ወጦችን በማጋለጥ በኩል እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አድንቀው፤ ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
በተለይ ወጣቶች አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ ለመዲናዋ ሰላም መጠበቅ እያበረከቱት ያለውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.