የፀጥታ አካላትን ተግባር ማጣጣል እና ለራስ ዓላማ ለማዋል መሞከር ተገቢነት የለውም -ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታ አካላት ከህዝብ ጋር በመተባበር እያከናወኑ የሚገኙትን ውጤታማ ተግባር ማጣጣል እና ከእውነት በመሰወር ለራስ ዓላማ ለማዋል መሞከር ተገቢነት እንደሌለው የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳሰበ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት የንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ በህዝብ ጥቆማ የተገኙ ጥይቶች አስመልከቶ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የፀጥታ አካላት ከህዝብ ጋር በመተባበር እያከናወኑ የሚገኙትን ውጤታማ ተግባር ማጣጣል እና ከእውነት በመሰወር ለራስ ዓላማ ለማዋል መሞከር ተገቢነት የለውም!
አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት የንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ በህዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ከ1ሺህ 800 በላይ ጥይቶች እንደተያዙ ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ፖሊስ የፌስ ቡክ ገፅ እና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን መረጃው መተላለፉ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የፀጥታ አካላት ከህዝብ ጋር በመተባበር እያከናወኑ የሚገኙትን ውጤታማ ተግባር ለማጣጣል እና ትክክለኛውን መረጃ ከእውነት ሰውረው የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ውሸቶችን እና ሌሎች ተገቢነት የሌላቸውን ወሬዎች እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡
መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የተቋማቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ጦር መሳሪያ እንዲጠቀሙ ሊፈቀድላቸው እንደሚችል ይታወቃል፡፡
ነገር ግን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ ከተገኙት ጥይቶች መካከል ከ1ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት የቡድን መሳሪያ የሆነ የብሬን ጥይቶች ሲሆኑ እነዚህ ጥይቶች ሊገኙ የሚገባው በፀጥታ ተቋማት እጅ ብቻ ከመሆኑም ባሻገር ለተቋማት ጥበቃ አገልግሎት በፍፁም የማይፈቀዱ በመሆናቸው ይህንን በምርመራ ለማጣራት እና ለማረጋገጥ ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ ማጣጣል እና ህዝብ በፀጥታ ስራ ላይ እያደረገ የሚገኘውን ተሳትፎ ዋጋ ማሳጣት አግባብ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ያምናል ፡፡
በወቅቱ በቁጥጥር ስር የዋለው የንብረት ግምጃ ቤቱ ሰራተኛም የክላሽ-ኮቭ ጥይቶች ናቸው ተብሎ በመዝገብ ፈርሞ እንደተረከበ ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
በብረበራው ወቅት የተቀረፀውን ምስልም ከዚህ ፅሁፍ ጋር የለጠፍነው እውነትን ክደው የሃሰት ወሬ እየፈበረኩ ህዝብን ለማደናገር የሚፈልጉ አካላትን ሴራ ለማጋለጥ ጭምር በመሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች ለሃሰት መረጃዎች ጆሮ ሳትሰጡ መረጃ እና ጥቆማችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የዘወትር ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
https://www.facebook.com/fanabroadcasting/videos/395183372389871