በአማራ ክልል ከህልውና ዘመቻው በተጓዳኝ የደረሰ ሰብል እየተሰበሰበ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከህልውና ዘመቻው በተጓዳኝ በመኸር ወቅት በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት የለማ ሰብል ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
እየተሰበሰበ ያለው ቀድሞ የደረሰ ገብስ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬና በርበሬ መሆኑን በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተለይ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ እንዲሁም በአዊ ዞን በኩታ ገጠም እርሻ የለማ ከ91 ሺህ ሄክታር በላይ ስንዴ ሰብል ለመሰብሰብ 132 ኮምባይነሮች እየተመቻቹ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
“በእስካሁኑ እንቅስቃሴም 49 የማጨጃና የመውቂያ እንዲሁም 50 የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖች ለአርሶ አደሩ ቀርበው አገልግሎት ጀምረዋል”ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ አርሶ አደሩ የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን የደረሰ ሰብል ፈጥኖ እንዲሰበስብ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የምዕራብ አማራ ሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ መልሴ በበኩላቸው፥ በአካባቢው ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ያለው ዝናብ ሊጥል ስለሚችል አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ የደረሰ ሰብል ፈጥኖ በመሰብሰብ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያስከትለው ጉዳት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለይ ዘግይተው ለተዘሩና በቀሪ እርጥበት ለተዘሩ ሰብሎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አቶ ንጋቱ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል በ2012/2013 የምርት ዘመን ከለማው መሬት 110 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን፥ በ2013/2014 የምርት ዘመን 4 ሚሊየን 384 ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል መልማቱ ተመላክቷል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!