Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የተደቀነውን አደጋ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ዛሬውኑ መነሳት አለብን – የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተደቀነውን አደጋ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ዛሬውኑ መነሳት አለብን ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ አመራሩ ከፊት በመሰለፍ ዘመቻውን ለመምራት መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግንባር ሆነው ዘመቻውን እንደሚመሩ ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላትም በግንባር በመሰለፍ የመሪነት ኃላፊነታቸውን እንዲሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንደሚሉት፥ በኢትዮጵያ የተደቀነው ወቅታዊ አደጋ ውስብስብና በርካታ ተዋንያኖች እየተሳተፉበት ነው፡፡

በተለይ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት አሸባሪው ህወሓትን ከጀርባ በመጋለብ የአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማንበርከክ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በዚህም አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ እድሉን ካገኘ በሁሉም አካባቢዎች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ተመሳሳይ ግፍ እንደሚፈጽም ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን የተደቀነውን አደጋ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት መነሳት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌላኛዋ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው አደጋው ኢትዮጵያን እንደመግቢያ በር በመጠቀም በመላው የጥቁር ህዝቦች ላይ የተቃጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በህልውናዋ ላይ የተቃጣ አደጋ ሲገጥማት ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን አባቶች በመስዋዕትነት ኢትዮጵያን እስካሁን ማቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ፈለግ በመከተል ወቅቱን የሚመጥን ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

አሸባሪው ህወሓት በምዕራባውያን ሚዲያዎች ጭምር እየታገዘ የከፈተው ጦርነት ሁለንተናዊና አገር የማፍረስ ግብ ያለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው፡፡

“አገር የሌለው ህዝብ የትም መኖር አይችልም” ያሉት አቶ አሻድሊ ከዚህ አኳያ የገጠመንን ፈተና በአግባቡ በመገንዘብ አገር ለመታደግ መነሳት አለብን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል የመወጣት አቅም እንዳላትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.