የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በትኩረት በማከናወን የሕዝብ መጻኢ ዕድሎች እንፈጥራለን – ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ጦርነት ጎን ለጎን የሕዳሴ ግድብ መደበኛ ግንባታና ኃይል የማመንጨት ሥራን በመሥራት የሕዝብ መጻኢ ዕድሎች እንፈጥራለን ሲል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጀነር ሀብታሙ ኢተፋ ለኢፕድ እንደገለጹት÷ የሕዳሴ ግድብ መደበኛ ግንባታው ሳይስተጓጎል ኃይል የማመንጨት ሥራ ጎን ለጎን እየተገነባ ነው ጠላትንም በመዋጋት የሕዝብ መጻኢ ዕድሎችን ለማስፋት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ÷ የሕዳሴ ግድብ መደበኛ ግንባታና ተጓዳኝ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ፤ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በመጠናቀቁም በተያዘው ውሃ ከ600 እስከ 700 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግድቡን ለመገንባት የቻለውን በማበርከት ግድቡ ያለበትን ደረጃ ለመስማት እየጠየቀ ነው ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ÷ የኅብረተሰቡን ጉጉት እውን ለማድረግ ጥቂት የኤሌክትሮ ሜካኒክ ሥራዎችን በማጠናቀቅ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የተያዘው የውሃ መጠን ኃይል ማመንጨት ሲጀመር የነበረውን የመብራት መቆራረጥ ከመቅረፉም ባሻገር ተጨማሪ ኃይል ያስገኛል ብለዋል፡፡
የኃይል አመንጪ ተርባይኖችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ÷ በቀጣይ ክረምት ተጨማሪ የውሃ መጠን ለመያዝ የሚያስችል ቦታ ለማዘጋጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
የግድቡን መገንባት ተከትሎ በርካታ ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው አገሪቱ ኃይል እንዳታመነጭ፣ የኢትዮጵያ እናቶች ከእንጨት መልቀም እንዳይላቀቁ፣ ትውልዱ እንዳይለወጥ ከመሻት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ÷ አሁን ላይ የግድቡ እውን መሆን ምኞታቸውን አጨልሟል ብለዋል፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድሎችን ይዞ ይመጣል ፤ ስኬታማ መሆኑ የማይቀር ቢሆንም በአጋጣሚው የኢትዮጵያ ዘመድና ጠላት ለመለየት አስችሏልም ነው ያሉት፡፡
መንግሥት በቁርጠኝነት ግድቡን ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት በመሆኑ መደበኛ ግንባታው ለአፍታም አልተቋረጠም ብለዋል ፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት በጠላት የተከፈተውን ጦርነት እየተዋጋ የሕዝብን መጻኢ እድል ለመገንባት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!