የፓን አፍሪካኒዝም መሠረቱ ኢትዮጵያኒዝም ነው – አስናቀ ሲሳይ
አዲስ አበባ፣ህዳር 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓን አፍሪካኒዝም መሠረቱ ኢትዮጵያኒዝም ነዉ ሲሉ የአፍሪካ እና መካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች ተመራማሪ አስናቀ ሲሳይ ገለጹ።
የዛሬውን የአውሮፓ ኅብረት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የወለደው ምዕራባዊያኑ በበርሊን ኮንፈረንስ ላይ የደረሱበት የስምምነት ሰነድ ነው ሲሉም ተመራማሪው አስረድተዋል።
ተመራማሪው አቶ አስናቀ ሲሳይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ፥ አውሮፓውያን ከበርሊን ኮንፈረንስ በኋላ ለኢንዱስትሪ ግብዓቶቻቸው የሚውሉ ጥሬ ቃዎችን ለመዝረፍ እንዲያመቻቸው አፍሪካን እንደቅርጫ በመከፋፈል ቅኝ ለመግዛት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተመራማሪው ÷ የዛሬው የአውሮፓ ኅብረት አፍሪካን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥር ለማዋል የሚሰራ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፥ ኅብረቱን የበርሊን ኮንፈረንስ “ውላጅ” ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ኢትዮጵያ ÷ የቀድሞውን የበርሊን ኮንፈረንስ ውሳኔ የሰበረች ብቸኛ ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ተመራማሪው ፥ ምዕራባውያን በዓድዋ ጦርነት መሸነፋቸውን ተከትሎ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ስለ ነፃነታቸው እንዲያስቡና እንዲታገሉ ማድረጓን ጭምር ነው ያብራሩት።
አቶ አስናቀ አክለውም ፣ የፓን አፍሪካኒዝም መሰረቱ ኢትዮጵያኒዝም ነው፣በኢትዮጵያኒዝም ኢምፔሪያሊዝም እና የአፓርታይድ አገዛዝ መሸነፉን፤ በዚህም የነጮች የበላይነት እና የቅኝ ግዛት ፖሊሲ መቀልበሱን ነው በአጽንኦት ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ ÷ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት አፍሪካን አንድ ማድረግ እንደቻለች የሚናገሩት ተመራማሪው፣ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በጽኑ አቋሟና በአልገዛም ባይነቷ ከድሮ ጀምሮ የምዕራባውያን ስጋት ሆና መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ስለ አፍሪካ አንድነት የሚታገሉ የአፍሪካ መሪዎች ÷ በምዕራባውያኑ ተቀባይነት ካለማግኘታቸውም በላይ መሪዎቹ በመፈንቅለ መንግስት እንደሚወገዱ፥ ባስ ሲልም ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡
እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ቶማስ ሳንካራ እና ሌሎች ስለ ጥቁር ህዝቦች የሚሟገቱ መሪዎች በምዕራባውን ግድያ፣እስራት እና እንግልት እንደደረሰባቸውም ነው ያወሱት፡፡
በመሆኑም የምዕራባውያንን እሳቤ ከግንዛቤ በማስገባት፥ ኢትዮጵያ የያዘችውን የህልውና ዘመቻ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አካል በማድረግ ሌሎች የአፍሪካ እና የመላው ዓለም ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!