የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በአየርላንድ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በአየርላንድ መዲና ደብሊን ተካሄደ።
ሰልፉ ‘ደብሊን ሲቲ ሴንተር’ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ነው የተከናወነው።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በአየርላንድ ደብሊን፣ ኮርክ፣ ጋሎዌይና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የአየርላንድ ዜጎች መሳተፋቸውን ‘ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ’ የተሰኘው ግብረ ሃይል አባል ወይዘሮ ራሔል ዳልተን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን እንደማይቀበሉና እጃቸውን እንዲያነሱ ሰልፈኞቹ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን ተገቢ ያልሆነና ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
የአየርላንድ በተለይም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይሞን ኮቬኔይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰጧቸው አስተያያቶች የተሳሳቱና ሊታረሙ የሚገባቸው መሆኑን ሰልፈኞቹ መግለጻቸውን ነው ወይዘሮ ራሔል ያነሱት።
ሰልፈኞቹ የአየርላንድ መገናኛ ብዙሃን በተለይም ‘አርቲኢ ኒውስ’ እና ‘አይሪሽ ታይምስ’ በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያወጧቸውን አፍራሽና አድሏዊ ዘገባዎችን ማውገዛቸውንና ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ገልጸዋል።
በሰልፉ ‘በቃ’ ወይም ‘#NoMore‘ መፈክሮች መስተጋባታቸውንና በአየርላንድ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ በአየርላንድ የሚኖሩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
ከሰልፉ ባለፈ ለአየርላንድ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የማስረዳትና ለፓርማላ አባላት ደብዳቤ በመጻፍ የመሞገት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ወይዘሮ ራሔል የተናገሩት።
በቅርቡም ዳያስፖራው ከ100 በላይ ለሚሆኑ የአየርላንድ ፓርላማ አባላት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ደብዳቤ ማስገባቱን አስታውሰዋል።
በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያያን ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!