ትዊተር የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅ የሆኑና እውነትን ለዓለም ለመግለጥ የሚሰሩ አካውንቶችን ድምፅ እያፈነ ነው ሲሉ ጋዜጠኞች ቅሬታ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትዊተር የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅ የሆኑና አሁን ላይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እውነቱን ለዓለም ለመግለጥ የሚሰሩ አካውንቶችን በማገድ ድምፃቸውን እያፈነ ነው ሲሉ ጋዜጠኞች እና የማህብረሰብ አንቂዎች ቅሬታ አቀረቡ።
መቀመጫዋን አሜሪካ አድርጋ በሙያዋ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ለኢትዮጵያ የላቀ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችውጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ፥ ትዊተር የኢትዮጵያውያንን ሃሳብ ዒላማ ባደረገ መልኩ አፍኗል ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች፡፡
በኤርትራ የማኅበረሰብ አንቂ እና የኢትጵያና የኤርትራ ወዳጅ የሆነው ስምኦን ተሥፋማርያም በበኩሉ ÷ ትዊተር እየፈጸመ ያለው ኢ-ፍትሃዊ ተግባር በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ላይ እምነት እንዲያጣ ማድረጉን ገልጿል፡፡
ስምኦን፥ ትዊተር በማኅበራዊ ገጹ ንቁ ሆነው የሀገራቸውን እውነት ለመግለጥ የሚንቀሳቀሱ ኢትጵያውያንን እና ኤርትራውያንን እንዲሁም የደጋፊዎቻቸውን ድምጽ አካውንታቸውን በመዝጋት አፍኗልም ነው ያለው፡፡
በትዊተር የተዘጉት አካውንቶች በማኅበራዊ የትሥሥር ገጹ ምህዳር ላይ እውቅናን ያተረፉ በኢትዮጵያና የኤርትራ እውነታን ለህዝብ በመግለጥ የሚታወቁ ነበሩም ተብሏል፡፡
የታገዱት አካውንቶች ÷በኢትዮጵያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን የህወሓት ቡድን የሚያወግዙ እንደነበሩም ነው የተመላከተው፡፡
አካውንቶቹ፥ በምዕራባውያን ተጽዕኖ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ እና #Nomore / “በቃ” በሚል ሃሽ ታግ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍልን በመድረስ እና በማንቃት ተጽዕኖ የፈጠሩ እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡
የኢፌዴሪ መንግስት ትዊተር ኢትዮጵያን የሚደግፉ እና የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ውሸት እና የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የሚያጋልጡ አካውንቶችን ዒላማ በማድረግ ዘግቷል የሚል ዕምነት እንዳለው መግለፁ ይታወሳል፡፡