የ3 ቢሊየን ብር የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አልፋና ካፒታል ከተሰኙ የኢንጂነሪንግ እና ዕቃ አቅራቢ ተቋማት ጋር የ3 ቢሊየን ብር የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ በከተሞች ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማሻሻል ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡
ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብና በተጠበቀው የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአምቦ፣ ነቀምቴ እና አሶሳ ከተሞች የሚከናወነው ፕሮጀክቱ በከተሞቹ የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በማዘመንና በማጠናከር የአገልግሎቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ ያስችላል፡፡
በመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ፕሮጀክቱ 325 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ መስመር የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተመላክቷል፡፡
ይህም የኔትወርኩን አቅም ከማሳደግ ባለፈ የኃይል መቆራረጥ እና የቴክኒክ ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም 235 ትራንስፎርመሮች ላይ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ የሚከናወን ሲሆን ÷ ከእነዚህ ውስጥም 70 በአምቦ፣ 121 በነቀምቴ እና 44 በአሶሳ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡
በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቀው ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ3 ቢሊየን ብር ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡