ገበታ ለሀገር …
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅና የሀገርን መዋዕለ ንዋይ በማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም አለው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተገነቡት የጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኙ ነው፡፡
ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ ሲሆን የተገነቡትም ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ፣ ስራ ለመፍጠር እና በዙሪያው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ በማለም ነው።
ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት እና በሚሊየን የሚቆጠሩ ሥራዎችን በመደገፍ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በሚያደርገው ቀጥተኛ አስተዋፅኦም በጎ የሆነው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው በጉልህ ይታያል።
በሀገራችን ኢትዮጵያም ቱሪዝም መንግሥት ላስጀመረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የማዕዘን ድንጋይ ሲሆን ከአምስቱ ቁልፍ ምሰሶዎች አንዱ ነው።
እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ ሥራዎች የቱሪዝም ዘርፉን ለማዳበር፣ ብዙ ጎብኝዎችን ለመሳብ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት፣ የስራ እድሎችን ለመፍጠር፣ መዳረሻዎችን ለማልማት እና ለማሻሻል ታልመው በሥራ ላይ በመዋል ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ በፊት በመሠረተ ልማት እጦት ከተጓዦች ተደብቀው የቆዩትን መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ስፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮች፣ እጅግ የተለዩ አዕዋፋት እና ዕጽዋቶችን በትስስሩ በተፈጠሩ ዕድሎች ለጎብኝዎችና አሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ነው።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሃብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ በመሆኗ በቱሪዝም መስኩ የምታደርገውን የማስተዋወቅና ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ገና ብዙ ማድረግ የሚጠበቅባት እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ በገበታ ለሀገር መዳረሻዎች የተገበረቻቸው ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በአቤል ነዋይ