አሸባሪው ህወሓት በህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት በየትኛውም የዓለም ክፍል ያልታየ ነው – የክልል ጤና ቢሮ ሀላፊዎች
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ መገልገያ የሆኑ የጤና ተቋማት የህዝብ ንብረቶች በመሆናቸው በየትኛውም ሀገር ጦርነት ሲከሰት ኢላማ ተደርገው እንደማያውቁ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ገለጹ፡፡
የሁለቱ የክልል የጤና ቢሮ ሃላፊዎች በፋና ቴሌቪዥን “ስለ ኢትዮጵያ” ፕሮግራም ላይ ተወያይተዋል።
አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሱት ውድመት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ህጎች ሳይቀር የጣሰ፣ ከሰብአዊነት የወጣ እና የአውሬነት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ እንደገለጹት በአማራ ክልል አሸባሪዎች በፈጸሙት ጥቃት 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺህ 850 የጤና ኬላዎች፣ 4 የደም ባንኮች፣ ለአፋር እና ለምስራቅ አማራ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ የኦክስጅን ማምረቻ ማእከል፣ 82 የሚደርሱ ጤና ጽህፈት ቤቶች፣ አንድ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የምርምር ማእከል ህንጻ ላይ ውድመትና ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ከዚህ ባለፈም የህክምና መሳሪያዎች እና መድሃኒቶች ተዘርፈዋል የቀሩት ደግሞ አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ተደርገው ወድመዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህ የማውደም እና የዘረፋ ተግባር ላይ የጤና ባለሙያዎች የገቡትን ቃለ መሃላ ወደጎን በመተው ተሳታፊ እንደነበሩ እና ይህም በጣም እንዳሳዘናቸው ዶክተር መልካሙ ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ ሳቢያም 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ገደማ ሰዎች የተመላላሽ ህክምናቸውን መከታተል እንዳልቻሉ፣ በቀን የወሊድ አገልግሎት ያገኙ የነበሩ 29 እናቶች አገልግሎቱን እንዳላገኙ፣ 96 ሺህ ህጻናት ክትባት ማግኘት እንዳልቻሉ፣ 98 ሺህ የኤች አይ ቪ ህሙማን ለወራት መድሃኒት እንዳላገኙ፣ 200 ሺህ የደም ግፊት ህሙማን መድሃኒት አለማግኘታቸው፣ በአሸባሪዎች የተደፈሩ 119 እናቶች እና ህጻናት የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቹም አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው የጤና ተቋማት ውድመት እንደ አማራ ክልል በአንድ እና በአጭር ጊዜ የተፈጸመ ሳይሆን ለውጡ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ቀስ በቀስ የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጤና ተቋማትን እንደምሽግ መጠቀም፣ አንዱ ሲጠገን ሌላውን የማውደም፣ የመዝረፍ፣ የልማት ስራዎች በተረጋጋ መልኩ እንዳይሰሩ ማድረግ እንዲሁም የተጀመሩ የጤና ተቋማት እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት መሆን በክልሉ ሲፈጸሙ ከነበሩ ጥቃቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አንስተዋል።
ሸኔ እና ህወሓት የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማይፈልጉ ምዕራባውያን ጋር በመመሳጠር ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ለማስቀረት በሚሰሩት የተላላኪነት ስራ እንደ አጠቃላይ በኦሮሚያ፥ በጤና ሚኒስቴር ደረጃ ተጣርቶ የተመዘገበ 413 የጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶበታልም ነው ያሉት።
ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ 38 አምቡላንሶች ከአግልግሎት ዉጭ እንዲሆኑ ወይም ለአሸባሪዎቹ አገልግሎት እንዲውሉ መዘረፋቸውንም አውስተዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በክልሉ የጤና ዘርፍ ያስከተለው ችግር ክትባት ስርጭት ላይ እንቅፋት በመፍጠሩ ወረርሽኝ መከሰቱን ጠቅሰው፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡ አምርቶ እንዳይበላ በመደረጉ የምግብ ዕጥረት ችግር መኖሩን ገልጸዋል።
በዚህም በተለይ ህጻናት ላይ እስከሞት የሚያደርስ ከፍተኛ ችግር መከሰቱንም ነው የተናገሩት።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!