ማህበሩ በተዋልዶ ጤና ላይ ያተኮረ የ44 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተዋልዶ ጤና ላይ የሚተገበር የ44 ሚሊየን ብር ፕሮጀክትን እቅዶ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ገለጸ።
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሀብቴ ÷ በጦርነት ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳይ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
ይህንንም ችግር በመረዳት በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልል የሚተገበር የ44 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ታቅዷል ።
የዚህ ፕሮጀክት ገንዘብ ከረጂ ድርጅቶች የተገኘ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፥ ፕሮጀክቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች መሠረታዊ የተዋልዶ ጤና ችግርሮችን የሚፈታ ይሆናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ማህበሩ ከሰራተኞች መዋጮ እና ከውስጥ ገቢው የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች እገዛ አድርጓል።
ለአፋር ክልል 1 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሣቁሶች ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ 2 ሚሊየን ብር በካሽ እንዲሁም 1ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሣቁሶች ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግማሽ ሚሊየን የሚገመት ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ውድመት በቦታው ተገኝቶ በማየት ግማሽ ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍም አድርጓል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ በጦርነቱ ምክንያት በሰሜን ምስራቅ አካባቢ የማህበሩ ስድስት ክሊኒኮች ወድመዋል፤ስድስት መኪኖች ተዘርፈዋል።
ማህበሩ እስከ 22 ሚሊየን ብር የሚገመት ወድመት ቢደርስበትም ለማህበረሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ አይቋረጥም ነው ያሉት።
በአለባቸው አባተ