ኢትዮጵያ ያካሄደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ነጻ ነበር – ብፁዕ አቡነ አንቶኒ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀመንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ኢትዮጵያ ያካሄደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ሰላማዊ፣ ነጻና የተረጋጋ ነበር አሉ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በብፁዕ አቡነ አንቶኒ የተመራውን ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ውይይቱን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፤ ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ኢትዮጵያ ምርጫውን በስኬት በማጠናቀቋ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጿል።
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ላለው ጥልቅ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትስስር አጽንኦት በመስጠት፤ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ ክርስቲያናዊ ቅርስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች በሩሲያ የስነ መለኮት ተቋማት ትምህርታቸውን መከታተላቸው ተቋማዊና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ጠንካራ ትስስር በሀገራቱ መካከል ላለው ሰፊ ትብብር አስተዋጽኦ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜና ታሪካዊ ግንኙነት ያሰመሩበት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።