Fana: At a Speed of Life!

የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማትን የሚያሳልጥ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው- ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማትን የሚያሳልጥ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ።

 

በሀዋሳ ከተማ ለአራት ቀን ሲካሄድ የቆየው የሚኒስቴሩና የክልሎች የ2014 በጅት ዓመት የስድስት ወራት የስራ ዕቅድ አፈጻጸም  ግምገማና የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

 

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ሚኒስትሯ እንዳሉት÷ በአገሪቱ በሁሉም ዘርፎች መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ራዕይ ተሰንቆ እየተሰራ ነው።

ከዚህ አኳያ ከሥራና ክህሎት ዘርፍ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ ገልጸው÷በተለይ አገራዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን ከሰለጠነ የሰው ኃይል ውጭ ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

የዘርፉ የስልጠና ስርአት የገበያው ትኩረትና ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን በሚኒስቴሩ ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጥናቱን ሥራ ላይ በማዋል ለሥራ ፈላጊ ዜጎች በአጫጭርና በመደበኛ ፕሮግራም በንግድ ክህሎትና በአስተሳሰብ ለውጥ እና  ተግዳሮቶችን ወደ መልካም ለመለወጥ በሚያስችሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎች  ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል።

“ለእዚህም በ1 ሺህ 800 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ የስልጠና ስርዓት በመዘርጋት አገራዊ ራዕይን የሚያሳካ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ይሰራል” ብለዋል ሚኒስትሯ።

ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተያዘውን አቅጣጫ ተፈጻሚ ለማድረግ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትን ጨምሮ የለውጥ ሀሳቦችን ወደ መሬት ለማውረድ ያስችላሉ የተባሉ ተቋማትን የመለየት ስራ እንደተከናወነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማትን ለማሳለጥና በየደረጃው ለኢኮኖሚው ብቁ የሆነ የሰው ሃይል  ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ  የተናገሩት።

በቴክኖሎጂ ሽግግር በኩልም ያየናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ” ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት÷ከዚህ በመነሳት አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.