ግማሽ ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በገቢዎች ሚንስቴር የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ የነበረ ግለሰብ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምቶ ግማሽ ሚሊየን ብርን በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
መላኩ ሸዋረጋ የተባለው ገለሰብ፥ በገቢዎች ሚንስቴር አዳማ ቅርንጫፍ የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ 1 ሚሊየን ብር በባንክ አካውንቱ እንዲገባለትና 500 ሺህ ብር ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ካፒታል ሆቴል ገንዘብ ሲቀበል የተገኘው ተከሳሽ በፈፀመው ጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወስኖበታል ነው የተባለው።
ተከሳሹ የስራ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ኽርበርግ ሮዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ድርጅት የ2 ዓመት የንግድ ስራ ትርፍ ግብር ብር 66 ሚሊየን 616 ሺህ 818 ብር ከ 93 ሳንቲም እንዲከፍል ሲወሰንበት የድርጅቱ የአስተዳደር ሰራተኛ የሆነችው 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር በውሳኔው ላይ ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ቅሬታ ማቅረቧ ተገልጿል፡፡
ተከሳሹ በበኩሉ የቀረበውን ቅሬታ ውሳኔውን ዝቅተኛ በሆነ መልኩ መወሰን እንደሚቻልና ለዚህም 1 ሚሊየን ብር በባንክ ለመቀበልና ቀሪውን 500 ሺህ ደግሞ እጅ በእጅ ለመቀበል ከተደራደረና ከተስማማ በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም 500 ሺህ ብሩን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል፡፡
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በ1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ መላኩ ሸዋረጋ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ተከሳሽ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሰውን የጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል አለመፈፀሙን ክዶ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ 4 የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ የድርጊቱን መፈፀም በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሹም ክስና ማስረጃዎቹን ማስተባበል ባለመቻሉ ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል ነው የተባለው፡፡
ወንጀለኛው በ4 ዓመት ከ10 ወር ፅኑ እሥራት እና በ2 ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በጉቦ የተሰጠው ገንዘብ ለተበዳይ እንዲመለስ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ገንዘቡ ለተበዳይ እንዲመለስ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!